









የቤንች ማጂ ልማት ማህበርን ሁሉ አቀፍ ተደራሽነት ለማስፋትና ለማጠናከር እንሰራለን ፦ ክቡር አቶ ሀብታሙ ካፍትን
የቤንች ሸኮ ዞን አስተባባሪ ኮሚቴ ከቤንች ማጂ ልማት ማህበር የበርድ አመራሮችና የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር በአጠቃላይ ስራዎችና በቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጨነቁ ኮንታር ለዞኑ አስተባባሪ ኮሚቴ የልማት ማህበሩን የ26 አመታት ጉዞ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ባለፉት 26 አመታት የልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ጉዞው በትምህርት ፣ በጤና ፣ በንጹህ መጠጥ ውሀ ፣ በመንገድ ከፈታ ፣ በኢኮኖሚ አገልግሎት ከ170 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ህዝቡ ማውረዱን ገልጸዋል።
ልማት ማህበሩ አጋር ድርጅቶችንና ከልማት ማህበሩ አባላትና በራስ አገዝ ፕሮጀክት በሚያገኘው ገቢ ከ80 በላይ አማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ቤቶች ፣ የኩላ ጋቻ ጤና ጣቢያ ፣ የግዝ መሬት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ የህዳሴ እና የኩሽት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፣ የሚዛን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና የቤተ መጻህፍት ግንባታዎች ፣ የጤና ኬላ ፣ በሼይ ቤንችና ሰሜን ቤንች ወረዳ የማህበረሰብ አቅም ግንባታ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በቅርቡ ወደ ስራ የገባው የባለ ልዩ ተሰጥኦ አዳሪ ትምህርት ቤት ፣ በደቡብ ቤንች ወረዳ ከJSI ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ማሻሻያ ስራዎች በርካታ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን ጠቁመው በተያዘው በጀት አመትም የአዳሪ ትምህርት ቤት የገቢ ማሰባሰቢያ ስራን ማጠናከር ፣ የህዝብ የመድኃኒት ቤት አገልግሎት ፣ በኮሜርሺያል የደን ልማት መሰል ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አጽናኝ ፈለቀ የአዳሪ ትምህርት ቤቱን የስራ ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት ትምህርት ቤቱ በ2015 የትምህርት ዘመን ከዞኑ ሁሉም መዋቅሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 50 ባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ስራውን መጀመሩን ገልጸዋል። በዚህም ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ማደሪያ ፣ ምግብና ውሀ ፣ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደርና ደቡብ ቤንች ወረዳ የመምህራን ደመወዝ ፣ ልማት ማህበሩ ዩኒፎርም ፣ የትምህርት ቁሳቁስና የትራንስፖርት ተሽከርካሪ ኪራይ በመፈጸም በቅንጅት ሲመራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በ2016 ተጨማሪ 52 ተማሪዎች በመቀበል ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ማስገባቱን የገለጹት አቶ አጽናኝ አሁን ላይ በህመምና በማህበራዊ ችግር ያቋረጡትን ሳይጨምር በድምሩ 96 ተማሪዎች በአዳሪ ትምህርት ቤቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በአጠቃላይ የውጤት ትንተና 67 ተማሪዎች ከ85 በላይ ፣ 21 ተማሪዎች ከ75-84 ፣ 4 ተማሪዎች ከ60-74 እንዲሁም 3 ተማሪዎች ከ50-59 አማካይ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል።
ለ2017 የትምህርት ዘመን 50 አዲስ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎችን በመቀበል ዝግጅት እንደሚደረግ የገለጹት አቶ አጽናኝ ለበጀት አመቱ የስራ ማስኬጃ ከ6.6 ሚሊየን ብር በላይ የበጀት ዕቅጅ መያዙን ገልጸዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እንደተናገሩት ልማት ማህበሩ አንጋፋና በርካታ የመንግስት የልማት ክፍተቶችን እየሸፈነ እዚህ የደረሰ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የአባላት ተሳትፎው አሁንም የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ገልጸው በቀጣይ በሁሉም መዋቅር የሚገኙ አመራሮች ፣ ፐብሊክ ሰርቫንቱንና አጠቃላይ ነዋሪውን የልማት ማህበሩ አባል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ልማት ማህበሩ ዘላቂ የሀብት ማስገኛ ስራዎች ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ የገለጹት አመራሮቹ ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ ስራም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። ሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ልማት ማህበሩን በቋሚነት ሊደግፉ ይገባል ያሉት አመራሮቹ የአባላት ማፍራት ስራውም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የልማት ማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት ሁላችንም ባለንበት መዋቅርና አመራርነት ለህዝባችን የሚጠቅሙ ተግባራትንና አሻራችንን ልናሳርፍ ይገባል ብለዋል። ለልማት ማህበሩ ቋሚ ገቢ ማስገኛ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ወደ ስራ መግባት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአባላት ማፍራት ስራውን እንደ ዞን በንቅናቄ መልክ ልንሰራ ይገባል ያሉት አቶ ሀብታሙ የህዝብ መድኃኒት ቤት ጊዜ ሳይሰጠው ወደ ስራ ሊገባ ይገባል ብለዋል። ልማት ማህበሩ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ሁሉም የዞኑ ነዋሪ አባል በመሆን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።