






የቤንች ማጂ ልማት ማህበር አዲስ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ከሚገቡ የተማሪ ወላጆች ጋር ውይይት አካሄደ።
ሚዛን አማን ፣ ጥቅምት 3/2016 የባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪ ወላጆች ልማት ማህበሩ ትውልድ ለማፍራት እየሰራ ባለው ስራ አሻራቸውን እንደሚያሳርፉና ከጎኑ እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር አዲስ ወደ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎች አዳሪ ትምህርት ከሚገቡ ተማሪዎችና ወላጆች ጋር በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውይይት አድርገዋል። በ2016 የትምህርት ዘመን 52 በመግቢያ ፈተና እንዲሁም 2 በልማት ማህበሩ ቦርድ ውሳኔ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ መቀላቀላቸውን የልማት ማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አጽናኝ ፈለቀ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልፀዋል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ላለፉት 27 ዓመታት ገደማ በትምህርት ፣ በጤና ፣ በመሰረተ ልማት ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ በአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ለዞኑ ህዝብ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል። በ2015 የባለ ልዩ ተሰጥኦ አዳሪ ትምህርት ቤት ስራን 50 ተማሪዎችን በመቀበል የጀመረ ሲሆን ለ2016 የትምህርት ዘመን ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች 54 ተማሪዎችን መቀበሉን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የአባላቱን ቁጥር በማሳደግና ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ በማድረግ የአዳሪ ትምህርት ቤቱን ግንባታ ጨምሮ በርካታ የልማትና የሰብአዊ አገልግሎት ስራ እንደሚሰራ ገልጸው የዞኑ ህዝብ ፣ አልሚ ባለሀብቱ ፣ ምሁራን ፣ ወጣቶችና መንግስት ሰራተኞች ከልማት ማህበሩ ጎን እንዲሰለፉ ጠይቀዋል።
በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ክትትልና ድጋፍ አስተባባሪ አቶ ታምራት ከበደ በበኩላቸው በተማሪዎች ስነ ምግባር ፣ በወላጆች ግዴታ ፣ በትምህርት ቤቱ አገልግሎትና ድርሻና በአጠቃላይ አሰራር ዙሪያ ለተማሪ ወላጆች የመወያያ ሰነድ አቅርበው ከተወያዩበት በኀላ የመግባቢያ ውል ሰነድ ሆኖ ተፈራርመዋል።
አስተያየት የሰጡ የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ባለ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ትምህርት ቤት ስራን ስንሰማ ቆይተናል ብለው ዛሬም በልማት ማህበሩ አማካኝነት ወደ ዞናችን መጥቶ ልጆቻችን በመቀላቀላቸው ተደስተናል ብለዋል።
በቀጣይ የልማት ማህበሩ ማህበሩ አምባሳደር በመሆንና ህዝቡ የልማት ማህበሩ አባል እንዲሆንና የድርሻቸውን እንዲወጣ እንሰራለን ብለው እንደ ወላጅ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
ልማት ማህበሩ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እየቀረጸ በመሆኑ የሁሉም አካላት እገዛ ፣ ድጋፍና ርብርብ ያስፈልገዋል ያሉት የተማሪ ወላጆች የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ በፍጥነት እንዲጀመርና እንዲጠናቀቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ስራው በፍጥነት እንዲከናወን ጠይቀዋል።