
















አዳሪ ትምህርት ቤቱ ብቁ ፣ ተወዳዳሪና በሀገር ግንባታ ውስጥ ሚና የሚኖራቸው ተማሪዎችን ለማፍራት ይሰራል ፦ ክቡር አቶ ቀበሌ መንገሻ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የልማት ማህበሩ የበላይ ጠባቂ
ሚዛን አማን ፣ ጥቅምት 15/2016 የቤንች ሸኮ ዞን የዞን ማዕከል ካቢኔና የየወረዳ አስተባባሪዎች የቤንች ማጂ ልማት ማህበር አዲስ ለገቡ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎች አቀባበልና በትምህርት ቤቱ ስራ ላይ ውይይት አድርገዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን የዞን ማዕከል ካቢኔ አባላት ፣ የ6 ወረዳና የ2 ከተማ አስተባባሪዎች የቤንች ማጂ ልማት ማህበር በ2016 ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት አዲስ ለገቡ 52 ተማሪዎች አቀባበልና በትምህርት ቤት ተገኝተው የጎበኙ ሲሆን በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የ2016 ዕቅድ ላይም ውይይት አድርገዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የልማት ማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ ቀበሌ መንገሻ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት ልማት ማህቀሩ ትውልድ ለመቅረጽና ሀገር ለመገንባት እየሰራ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የልማት ማህበሩ የቦርድ አመራሮችና ስራ አስኪያጆች አዳሪ ትምህርት ቤቱ እዚህ እንዲደርስ ትልቁን ኃላፊነት መወጣታቸውን ገልጸው ለሀገር በርካታ ዶክተሮች ፣ ኢንጂነሮችና ተመራማሪዎችን ለማፍራት እየሰራን ነው ብለው የዞኑ ህዝብ ፣ አመራሩ ፣ አልሚ ባለሀብቱና ባለድርሻ አካላት ከልማት ማህበሩ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አጽናኝ ፈለቀ በመድረኩ ባቀረቡት ለውይይት መነሻ ሰነድ ልማት ማህበሩ ዞናዊ የሰው ሀይል ልማት ላይ ብቃት ያለው ፣ ተወዳዳሪና የህብረተሰብ ችግር ፈቺ ዜጋ ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።
በ2015 በዞኑ 53 ባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎችን ይዞ ስራ የጀመረ ሲሆን 3 ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሲያቋርጡ 50 ተማሪዎች ተስፋ ሰጪና አበረታች የሆነ ውጤት አምጥተዋል ብለዋል። በ2016 የተሻለ ውጤት ያላቸውን 52 ተማሪዎች በመመልመል ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ መግባታቸውን ገልጸው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ፣ ሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በቁሳቁስ ፣ በመምህራን ፣ በምግብና መኝታ አገልግሎት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ ኬና በሰው ሀይል ልማት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። አመራሩ ፣ መንግስት ሰራተኛው ፣ አልሚ ባለሀብቱና መላው የዞኑ ነዋሪ የልማት ማህበሩ ተግባራት የራሱ አድርጎ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። አዳሪ ትምህርት ቤቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ በመድረኩ ማጠቃለያ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲና የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር አዳሪ ትምህርት ቤቱን በመደገፍ ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል። ደቡብ ቤንችና ሲዝ ከተማ አስተዳደር ቃል የገቡትን በተግባር አረጋግጠዋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ቀሪ ወረዳና ከተማ አስተዳደር ቃል የገቡትን በፍጥነት ገቢ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በመድረኩ ማጠቃለያ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በመገኘት የአዳሪ ትምህርት ተማሪዎች ማደሪያ ፣ መመገቢያ ህንጻዎችን የጎበኙ ሲሆን በዕድገት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ከተማሪዎች ጋር ትውውቅና በጋራ ፎቶ የመነሳት ፕሮግራም አካሂደዋል።
Quality education for next generation; I can see at BMDA.