








የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ከፊታችን ያለውን የመበልጸግ ተስፋ እውን ለማድረግ ልማት ማህበሩን ማጠናከርና ህዝባዊ መሰረቱን ማስፋት ያስፈልጋል ፦ ክቡር አቶ ጸጋዬ ማሞ
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር 6ኛ ዓመት መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በሚዛን አማን እያካሄደ ይገኛል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት የቤንች ማጂ ልማት ማህበር አንጋፋ ፣ የበርካታ ዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የፈታ እና የህዝብ አቅም ከጎኑ የነበረ የልማት ማህበር ነው ብለዋል።
ልማት ማህበሩ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል ያሉት ኃላፊው ህዝቡን ፣ ጉልበትን ፣ አባላትን በማሳተፍ የልማት ፍላጎቶችን ሟሟላትና ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ከፊታችን ያለውን የመበልጸግ ተስፋ እውን ለማድረግ ልማት ማህበሩን ማጠናከርና በዕውቀት መምራት ይገባል ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የልማት ማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ ሀብታሙ ካፍትን መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ባለፉት 28 አመታት በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና በአቅም ማጎልበት ስራዎች ከ170 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ህዝቡ ማውረዱን ገልጸዋል።
በተለይም ባለፉት አመታት በአለም አቀፍ የኮቪድ 19 እና ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የረጂ ድርጅቶች የፖሊሲ ለውጥና የአባላት ተሳትፎ መቀዛቀዝ ተፈጥሮ መቆየቱን ገልጸዋል። ከሀገራዊ ለውጥ ማግስቱ አደረጃጀቱን በአዲስ መልክ በማስተካከል ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት 3 አመታት በጤና ፣ በትምህርት ፣ በራስ አገዝ ፕሮግራሞች በርካታ ተግባራት መሰራታቸውን ገልጸው በቅርቡ ከ150 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመያዝ የባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎች አዳሪ ትምህርት ቤት ለመገንባት የሀብት ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በቀጣይም ህዝባዊ መሰረቱን ለማስፋት የአባላት ቁጥሩን መጨመርና ሁሉም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የቤንች ማጂ ልማት ማህበር የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጨናቁ ኮንታር በመድረኩ እንደተናገሩት የቤንች ማጂ ልማት ማህበር ከዛሬ 28 ዓመት በፊት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታትና የመንግስት የልማት ክፍተትን ለመሙላት የተቋቋመ ልማት ማህበር ነው ብለዋል።
ልማት ማህበሩ ከየትኛውም የፖለቲካ ውግንና ነጻ ፣ መንግስታዊ ያልሆነ የህዝብ ተቋም መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ህዝባዊ መሰረቱን ለማስፋትና በርካታ ፕርጀክቶችን እውን ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።